First time to EOPCW?

"የህዳሴው ግድብ የእኛ ነው!!" በሚል መሪ ቃል ውይይት ተካሄደ።

"የህዳሴው ግድብ የእኛ ነው!!" በሚል መሪ ቃል ውይይት ተካሄደ።

Posted on: 23 Mar,20

ግብጽ የህዳሴውን ግድብ ከተሳካላት በባለቤትነት ለማስተዳደር ካልተሳካላት ግን ለማኮላሸት ከአጋሯ አሜሪካ ጋር በመሆን ያዘጋጀችው በተንኮል የተሞላ የመደራደሪያ ሀሳብና ሰነድ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘቱን ተከትሎ "አቧራው ጨሰ" የጦር ጉሰማ እያሰማች ትገኛለች። ይህን "እኛ እንጠቀም እናንተ እየተራባችሁና እየተጠማችሁ ታረዙ የግብጾች የብልጣ ብልጥ አካሄድ" የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከሀገራዊና አለማቀፋዊ የሀብት አጠቃቀም ህግና መብት አኳያ በመዳሰስ ውይይት አካሄዷል። በዚህም ውይይት የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ጨምሮ የደሴ ከተማና የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች፣ የመንግስት ሰራተኞችና የማህበረሰቡ ተወካዮች እንድሳተፉ ተደርጓል። ውይይቱን አስመልክተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕርዜዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን የወሎ ህዝብ ያለውን ተካፍሎ የሚበላ ብቻ ሳይሆን መሬቱም ጣራውም ሳይሰስት አፈሩንና ውሃውን ለአባይና አዋሽ ወንዞች የሚያካፍል ለእኛ እንጅ ለእኔ ብሎ የማያውቅ ህዝብ የሚኖርባት ሀገር ልጆች በመሆናችን ዛሬም ቢሆን በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሀዊ የሀብት አጠቃቀም እንድኖር እንጅ ግብጾችን የመጉዳት ፍላጎቱ የለንም ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ ከንጉስ ሚኒሊክ ጀምሮ የአባይን ወንዝ ለልማት ለመጠቀም በኢትዮጵያውያን የተካሄደውን እንቅስቃሴ እያነሱ ግብጾች በወንዙ ላይ ግንባታው እንዳይካሄድ ሴራዎችንና ተንኮሎችን በመስራት የሀገሪቱን ሰላም ከማወክ በቀጥታ እስከመውረር የደረሰ እርምጃ የወሰደች ሀገር ማመን ከባድ ስለሚሆን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ውስጣዊ አንድነቱን ከማጠናከር ጀምሮ የጥላት ሀይል አሳፍሮ መመለስ የሚያስችል የመከላከያ ሰራዊት እና የኢትዮጵያውያንን ድምጽ ለዓለም የሚያሰማ ጠንካራ የውጭ ዲፕሎማሲ መዋቅር እንድዘረጋ ለማሳሰብ ጭምር መድረኩ ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል። በመድረኩም የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ በጋራ የመጠቀም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ህጋዊ ስምምነቶችና መብቶች የሚመለከቱና የህዳሴውን ግድብ ለማኮላሸት ግብጽ የተጠቀመችባቸውን በሸፍጥ የተሞላ ጂኦ ፖለቲካዊ ፣ ድፕሎማሲያዊ አካሄድና የሜድያ አጠቃቀም ሂደቷን የዳሰሱ ጽሁፎችን አቅርበዋል። በተጨማሪም የግብጾችን ቀረርቶና ፉከራ የገታ "ኢትዮጵያውያን በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት አላቸው" በማለት በይፋ መልስ ከሰጠችው ከጎረቢታችን ሰሜን ሱዳን ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች የሚያጠናክሩ የህዝብ ለህዝብ ፣ የምሁራንና የመሪዎች ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት ቀርቧል። የውስጥ ሽኩቻችንን እንደመልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ግብጽ የቻለችውን ሁሉ ከማድረግ አትቆጠብም ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ግብጽና አጋሮቿ ኢትዮጵያውያንን በብሄር፣ በሀይማኖትና በቋንቋ ለማተራመስ ስትራቴጂ ቀርጸው ገንዘብ መድበው ከመንቀሳቀስ ባለፈ ኢትዮጵያ የግብጽን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ስምምነቶችን ካልፈረመች ወረራ የሚያደርስ ዛቻ ማሰማቷ ከኋላ ታሪኳ አኳያ የሚጠበቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም ተሳታፊዎች ግብጽ ይህንን ንቄት የተሞላበት መግለጫ ለመስጠት የደፈረችው በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ እጇን አስረዝማ በመግባት ሆድ አደር የሆኑ ግለሰቦችን በገንዘብ ደልላ በብሄር፣ በቋንቋና በሀይማኖት አሳውራ በኢትዮጵያውያን መካከል በፈጠረችው የርስ በርስ ሽኩቻ ተማምና ሊሆን ስለሚችል ትውልዱ ሊነቃ ይገባዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ግድቡ የእኔ + የአንተ + የአንቺ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም "የእኛ ኢትዮጵያውያን" በመሆኑ ለገንዘባችን እና ለህይወታችን ሳንሰስት ለፍፃሜ እናደርሰዋለን፡፡