Posted on: 23 Mar,20
ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አርክቴክቸር ምህንድስና ትምህርት ክፍል ለአምስት አመት ተኩል ሲያስተምራቸው ከነበሩት ተማሪዎች ውስጥ መጋቢት 3 ቀን በዋለው ሴኔት ውጤታቸውን መርምሮ ሃያ ስድስት ተማሪዎችን በደማቅ ዝግጅት አስመርቋል፡፡ በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ኢትዮጵያ በኪነ ህንጻ ዘርፍ የቆዬ ጥበብ ባለቤት መሆኗን አስታውሰው ተማሪዎች በቆዩባቸው አመታት ከአካዳሚያዊ እውቀት ባለፈ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና ችረዋል፡፡ ዶ/ር መላኩ በ2012 ዓ.ም ከተመረቁት ሃያ ስድስት ተማሪዎች መካከል በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ሁለት ተማሪዎች በትምህርት ክፍሉ እና በማኔጅመንት ውሳኔ በተቋሙ ውስጥ በመምህርነት እንዲቀጠሩ መወሰኑን አብስረዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ የህይወት ምዕራፍ ሲሸጋገሩ ያገኙትን እውቀት እና ልምድ በተግባር በማዋል ዘርፉ ላይ ትልቅ አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ እንደሚገባ አሳስበው ምሩቃኑ በአገሪቱ ነባራዊ ሁናቴ ላይ በጎ አሻራ በማስቀመጥ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት መቻል እንዳለባቸው ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል፡፡ ዶ/ር አባተ ኢትዮጵያ ከጣራ ወደ መሰረት እነዲሁም ከአንድ ፍልፍል ደንጋይ ህንጻ በማዋቀር የቀደመ የጥበብ ተምሳሌት መሆኗን አውስተው ተመራቂ ተማሪዎች ራሳቸወን በማብቃት በአለም ገበያ ጭምር ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ም/ ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ የሱፍም በምረቃ ፕረግራሙ ወቅት በክብር እንግድነት ተገኝተው ለምሩቃኑ ንግግር አድርገዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም ትምህርት ዘመን ከአጠቃላይ ተመራቂዎች 3.67 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ኤደን ሽመልስ እና 3.54 ያመጣው ዳዊት ማለደ ወደ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መቀላቀላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው በቆይታቸው ባገኙት እውቀትና ልምድ ተቋሙን እና አገራቸው ለማገልገል ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡